Job 14

1“ከሴት የተወለደ ሰው፣
ዘመኑ ዐጭርና በመከራ የተሞላ ነው፤
2እንደ አበባ ይፈካል፤ ይረግፋልም፤
እንደ ጥላ ይፈጥናል፤ አይጸናምም።
3እንደዚህ ባለ ሰው ላይ ዐይንህን ታሳርፋለህን?
ለፍርድስ በፊትህ ታቀርበዋለህን?
ሰብዓ ሊቃናት፣ ቩልጌትና ሱርስት እንዲሁ ሲሆን ዕብራይስጡ ግን ታቀርበኛለህን? ይላል

4ከርኩስ ነገር ውስጥ ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል?
አንድ እንኳ የሚችል የለም!
5የሰው ዕድሜ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፤
የወራቱንም ብዛት ወስነህ አስቀምጠሃል፤
ሊያልፈው የማይችለውንም ገደብ አኖርህለት።
6እንግዲህ ዘመኑን እንደ ምንደኛ እስኪፈጽም ድረስ፣
ፊትህን ከእርሱ መልስ፤ ተወው።

7“ዛፍ እንኳ ቢቈረጥ፣
እንደ ገና ሊያቈጠቍጥ፣
አዳዲስ ቅርንጫፍም ሊያበቅል ተስፋ አለው።
8ሥሩ በምድር ውስጥ ቢያረጅ፣
ጕቶው በመሬት ውስጥ ቢበሰብስም፣
9የውሃ ሽታ ባገኘ ጊዜ ያቈጠቍጣል፤
እንደ ተተከለም ችግኝ ቅርንጫፍ ያወጣል።
10ሰው ግን ይሞታል፤ ክንዱንም ይንተራሳል፤
ነፍሱም ትወጣለች፤ ከእንግዲህስ የት ይገኛል?
11ውሃ ከባሕር ውስጥ እንደሚያልቅ፣
የወንዝ ውሃም ጠፍቶ እንደሚደርቅ፣
12እንደዚሁም ሰው ይተኛል፤ ቀናም አይልም፤
ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤
ከእንቅልፉም አይነሣም።

13“ምነው መቃብር
በዕብራይስጥ ሲኦል ማለት ነው።
ውስጥ በሰወርኸኝ!
ቍጣህም እስከሚያልፍ በሸሸግኸኝ!
ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣
ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ!
14ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል?
እድሳቴ
ወይም መፈታቴ
እስከሚመጣ ድረስ፣
ተጋድሎ የሞላበትን ዘመኔን ሁሉ እታገሣለሁ።
15ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤
የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ።
16በዚያን ጊዜ በርግጥ ርምጃዬን ትከታተላለህ፤
ነገር ግን ኀጢአቴን አትቈጣጠርም።
17መተላለፌ በከረጢት ይቋጠራል፤
ኀጢአቴንም ትሸፍናለህ።

18“ተራራ እንደሚሸረሸርና እንደሚወድቅ፣
ዐለትም ከስፍራው እንደሚወገድ፣
19ውሃ ድንጋይን እንደሚቦረቡር፣
ጐርፍም ዐፈርን ዐጥቦ እንደሚወስድ፣
አንተም የሰውን ተስፋ ታጠፋለህ።
20አንድ ጊዜ ፈጽመህ ትበረታለህ፤ እርሱም ያልፋል፤
ገጽታውን ትቀይራለህ፤ ትሸኘዋለህም።
21ልጆቹ ቢከበሩ አያውቅም፤
ቢዋረዱም አያይም።
22የገዛ አካሉ ሕመም ብቻ ይሰማዋል፤
ለራሱም ብቻ ያለቅሳል።”
Copyright information for AmhNASV